=<({አል-ኢኽላስ 112:1-4})>=
ﺑﺴﻢ ﺍﻟﻠﻪ ﺍﻟﺮﺣﻤﻦ ﺍﻟﺮﺣﻴﻢ
1. በል! እርሱ አላህ አንድ ነው።
2. አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው።
3. አልወለደም፤ አልተወለደምም።
4. ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም።
![]() =<({አል-ቁርአን 96:1-5})>=
![]() በቡኻሪ በተዘገበው ሐዲስ መሰረት እውቀትን መሻት በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው። ![]() |
---|
አሏህ የማንኛውም ነገር ፈጣሪ ፣ ሰጭ ፣ ነሽ ሲሆን አምልኮት ለእሱ ብቻ የሚገባ፤ እሱም ውብና ሙሉ የሆኑ ስምና ባህርያቶች ያሉት ጌታ ነው።
ከአሏህ ውጭ በሐቅ የሚመለክ አምላክ የሌለ መሆኑን እና ሙሐመድ የአሏህ እውነተኛ ባሪያና መልዕክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ። ልጆች ይህ አባባል ወይም አረፍተነገር ሸሃዳ ተብሎ ይጠራል። ሸሃዳ ማለት የምስክርነት ቃል ማለት ነው።
ልጆች አሏህ በዙርያችን የምናያቸው እና የማናያቸው ፍጥረቶች ጌታ ነው። ለምሳሌ የመላኢካዎች ፣ የጅኖች ፣ የሰዎች ፈጣሪ ነው። አሏህ መላኢካዎችን ከብርሃን የፈጠረ፤ ጅኖችን ከዕሳት የፈጠረ ጌታ ነው።
ልጆች ሁሉም መላኢካዎች አሏህን ይገዛሉ፤ ለእሱም ይሰግዳሉ። አልታዘዝም አይሉም ሁሌም ታዛዦች ናቸው። ነገርግን ከጅኒዎች በአሏህ የሚያምኑ ሙስሊሞች አሉ። ከጅኒዎችም አሏህን የማይገዙ ፣ አሏህን የማይታዘዙ ፣ በእሱም የማያምኑ ፣ መጥፎ ነገሮችን የሚሰሩ ፣ ሰዎችን ወደ መጥፎ ነገሮች የሚጣሩ አሉ። ታዲያ የነዚህ መሪ የሆነው ሸይጧን ነው።
አሏህ እኔን ፈጥሮኛል፤ አሏህ አንተንም ፣ አንችንም ፈጥሯችኋል። እናም አሏህ መላኢካዎችን እና ጅኖችን ፈጥሯቸዋል።
አሏህ ለእኛ ብዙ ነገሮችን ሰጥቶናል። ለሁሉም ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ሰጥቷቸዋል። አሏህ ለእኛ ህይወት ሰጥቶናል፤ መልሶም ይወስዳታል። አሏህ እምናይበት አይን ፣ እምንተነፍስበት አየር ሰጥቶናል። አሏህ እኛን በህይወት እንደሚያኖረን ሁሉ ሌሎች ሰዎችንም በህይወት እንዲኖሩና እንዲሞቱ የሚያደርጋቸው እሱ አሏህ ነው። ከላይ ያነበባችኋቸው ነገሮች በሙሉ የሚያመላክቱት ተውሂደ ሩቡብያ(አሏህ በጌታነቱ አንድ ብቻ) መሆኑን ነው።
ልጆች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሞክሩና ትክክል መሆናችሁን አረጋግጡ።
እነዚህን ጥያቄዎች በትክክል ከመለሳችሁ የአሏህን ጌታነት ተረድታችኋል ማለት ነው።
ልጆች አሏህ ሐሊቅ(ፈጣሪ) ነው። ሁሉንም ነገር የፈጠረው እርሱ ነው። ሰማያትን እና ምድርን እንዲሁም በውስጧቸው ያሉ ነገሮችን ሁሉ የፈጠረው እሱ አሏህ ነው። ሰባት ሰማያትን እና ሰባት ምድርን ፈጥሯል። ከሰባት ሰማዮች ውስጥ አንዱን እንጅ ሌሎችን አናያቸውም። ምክኒያቱም ሌሎቹ ያሉት እኛ ከምናየው ሰማይ በላይ ናቸውና። ከሰባቱ ምድሮችም እኛ ያለንበትን እንጅ ሌሎችን አናያቸውም።
አሏህ እኛ የምንተኛበትን ጊዜ ሌሊትን ፈጥሯል። የቀን ብርሃንንም ፈጥሯል። ፀሀይን ፣ ጨረቃን ፣ ከዋክብቶችን ውብ አድርጎ ፈጥሯቸዋል። ማን?……………አሏህ ተራራዎችን ፣ ኮረብታዎችን ፣ ባህሮችን ፣ ውቅያኖሶችን ፣ እንስሳቶችን ፣ ዛፎችን ፈጥሯል።
ልጆች ብርቱካን ፣ ሙዝ ፣ አበባ ትወዳላችሁ አይደል ታዲያ ብርቱካንን የፈጠረው ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ሙዝንስ የፈጠረው ማነው? አበባዎችን የፈጠረው ማነው? አሏህ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ነው ካላችሁ በትክክል መልሳችኋል።
ልጆች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሞክሩና ትክክል መሆናችሁን አረጋግጡ።
ልጆች ፀሀይን ባያችሁ ጊዜ ማን እንደፈጠራት አስቡ። ፀሀይ ሙቀት ትሰጠናለች። ምድር ላይ ያሉ ብዙ ነገሮች የፀሀይን ሙቀት ይፈልጋሉ። ሙቀቷንም ብርሃኗንም እንፈልጋለን።
ጨረቃ ሙሉ ሆና ባያችሁ ጊዜ ምን ያህል ቆንጆ እንደሆነች አስቡት። ጨረቃ የሯሷ መንገድ አላት፤ ፀሀይም የራሷ መንገድ አላት።
ከአሏህ ድንቅ ፍጥረቶች እነዚህ የምትመለከቷቸው ትልልቅ ተራራዎች ፣ ውቅያኖሶች ፣ ደመናው ፣ ዝናቡ ፣ የፏፏቴ ውሃ ፣ አበባዎች ፣ የአትክልት ቦታዎች ፣ በረሃው ፣ ባህሩ ፣ ጨረቃው ፣ ፀሀዩ እንዴት ያሉ የሚያስገርሙ የሚያማምሩና የሚያስደስቱ ፍጥረቶች እንደሆኑ ተመለከታችሁ? ጎበዝ ልጆች! ታዲያ የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ አሏህ ነው።
ልጆች አሏህ ይፈጥራልም ያስገኛልም። አሏህ ሐሊቅ(ፈጣሪ) እና ረዛቅ(ሰጭ) ነው። ከሰማይ የሚወርድ ዝናብ ይሰጠናል። የምንበላውን ምግብና መጠጥ ይሰጠናል። የምንሰማባቸውን ጆሮዎች ፣ የምናይባቸውን አይኖች ፣ የምንተነፍስበትን አየር እና ገንዘብ ሰጥቶናል።
ይህን ሁሉ ስላደረገልንም እናመሰግነዋለን እንወደዋለንም። እንወደዋለን ምክኒያቱም ፈጥሮናል፤ ብዙ ነገሮችንም ሰጥቶናል። እንወደዋለን ምክኒያቱም ሙስሊሞች አድርጎናል።
ልጆች አሏህን እንወደዋለን! ስለዚህ ያዘዘንን ነገር እንሰራለን። ከከለከለንም ነገር እንርቃለን። እሱንም ብቻ እንለምናለን። ይህ የአምልኮት ትርጉም ሲሆን ተውሂደል ኡሉህያ የአምልኮተ አሏህ አንድነት ተብሎ ይጠራል። በሌላ አገላለፅ አምልኮት የሚገባው አንድ አሏህ ብቻ እንደሆነ ማረጋገጥና ማመን ማለት ነው።
ልጆች አሏህን እንወደዋለን ምክኒያቱም አሏህ እጅግ በጣም አዛኝ ፣ ፍትሃዊ ነው። እንወደዋለን ምክኒያቱም ቆንጆ ስሞች አሉትና። እሱ ሁሉን ተመልካች፤ ሁሉን የሚያይ ነው። እንዲሁም እሱ ሁሉን ሰሚ ነው፤ ሁሉንም ነገር ይሰማል። ታዲያ እሱ ከሁሉም ነገር በላይ ከሆነ ከሰማይ ከዙፋኑ ላይ ነው ያለው። ሁሉንም ነገር ያውቃል። ውብ ፊት አለው ነገርግን እርሱን የሚመስል ምንም ነገር የለም። ይህ የስምና ባህሪያቶች ተውሂድ ነው።
ልጆች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሞክሩና ትክክል መሆናችሁን አረጋግጡ።
አሏህን ብቻ ነው የምንገዛው፤ አሏህንም ብቻ ነው የምንለምነው።
ሶላት ስንሰግድ ግንባራችነን እና አፍንጫችነን መሬት ላይ እንደፋለን አይደል ልጆች?
አዎ! ይህ ሱጁድ ተብሎ ይጠራል። ሱጁድ የምናደርገው ለአሏህ ብቻ ነው።
ልጆች አሏህን እንታዘዘዋለን፤ አናምፀውም። ምክኒያቱም አሏህ ስንታዘዘው ይወደናል። ስናምፀው አይወድልንም። ስንታዘዘው ብዙ ነገሮችን ካለን ነገር ላይ ጨምሮ ይሰጠናል። ሳንታዘዘው ስንቀር ግን ሊቀጣን ይችላል። ወይም ደግሞ እንዲምረን ከጠየቅነው ይምረናል። ምክኒያቱም መማር ይወዳል።
የተከበራችሁና የተወደዳችሁ ውድ ሙስሊም አባቶች ፣ እናቶች ፣ ወንድሞች እና እህቶች እንደ ምታውቁት ልጆች የነገ ትውልድ የኢስላም ተረካቢዎች ናቸውና ልጆቻችነን ወይም ታናሾቻችነን በኢማን ፣ በእውቀት ፣ በሐያዕ ፣ በትቅዋ እና በመለካም ባህሪያት ኮትኩተን ልናሳድጋቸው ይገባል። ይህም በእያንዳንዳችን ላይ የተጣለ ግዴታ ነው።
ታዲያ ይህን ለማድረግ ገና በለጋ እድሚያቸው የተለያዩ መፅሐፎችን እያነበብን ወይም ደግሞ ገዝተን በመስጠት ስለ ኢስላም እንዲያጠኑ ማድረግ እውቀት እንዲጨብጡ ማድረግ ይኖርብናል። ይችንም አንስ ያለች ተውሂድ ለልጆች የምትል ፅሁፍ ለልጆችዎ ፣ ለታናሽዎ ቁጭ ሲሉ በማስነበብም ይሁን በማስደመጥ ልጆቻችን በትክክለኛ አቂዳ ላይ ተኮትኩተው እንዲያድጉ እንሞክር።
ወሰላሙ አለይኩም ወረህመቱሏሂ ወበረካቱህ!
የወጣቱ ተልዕኮ አድራሻ
ኢስላማዊ መጽሐፎችን ያውርዱ |
---|